Click here for PDF
ኤፍሬም እሸቴ – በግል
ማክሰኞ ሚያዚያ 9/2004 ዓ.ም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ካቀረቡ በኋላ እንደተለመደው የምክር ቤቱ ክቡራን አባላት በንባብ ላቀረቡላቸው ጥያቄዎቻቸው መልስ ሲሰጡ ተከታትያለኹ። ከጥያቄዎቹ አንዱ ወቅታዊው የሙስሊሞች ጉዳይ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምላሻቸው “መንግሥት በሃይማኖት ውስጥ ጣልቃ አልገባም” የሚለውን በሰፊው ሲያብራሩ ቆዩ። አንዱ ማብራሪያቸው ስለ ሰላፊያዎች (አል-ሰላፊያ ወይም ወሐቢያዎች) ነው። ራሳቸውን “አል-ሰላፊዩን” የሚሉትና ትክክለኛውን የቁርዓን ትምህርት እንከተላለን የሚሉት የሙስሊም ክፍል የሆኑትና መሠረታቸውን በሳዑዲት አረቢያ ያደረጉት ጽንፈኛ ወገኖች በተቃዋሚዎቻቸው ደግሞ “ወሐቢያዎች” ይባላሉ። የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ስለ ወሐቢያዎች እና ስለአክራሪነታቸው ማተት ስላልሆነ የዚህን ቡድን አስተምህሮ እና በኢትዮጵያ ላይ ስለ ጋረጠው ከፍ ያለ አደጋ “አክራሪ እስልምና በኢትዮጵያ” (ኤፍሬም እሸቴ፣ በ2000 ዓ.ም/ 2008 የታተመ) የሚለውን መጽሐፍ ማንበብ እንደሚቻል በመጠቆም አልፋለኹ።
ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ሙስሊም አክራሪዎች ከማብራራታቸው ጎን ለጎን ደግሞ አክራሪነት በእስልምና ብቻ ያልተገታ መሆኑን ለማስረዳት በሚመስል መልኩ በክርስትናው ውስጥ በተለይም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ያለውን በምሳሌነት ለማንሣት በጥምቀት ወቅት ወጣቶች ይዘውት ወጡ ያሉትን መፈክር ጠቅሰዋል። “ጥምቀት ላይ ከነበሩት መፈክሮች አንዱ ‘አንድ አገር – አንድ ሃይማኖት’ የሚል ነው። …. ‘አንድ አገር – አንድ ሃይማኖት’ የሚል ሕገ መንግሥት የለንም። (መፈክሩ) … የክርስቲያን መንግሥት እንዲኖር የሚፈልጉ … እንዳሉ ያሳየናል” ብለዋል – ጠ/ሚኒስትሩ። “የዚህም መነሻው የግንዛቤ ማነሥ በመሆኑ በማስተማር የሚመለሱ ናቸው” ሲሉ አክለዋል።
ቀጥለውም ይኸው አክራሪነት በክርስትናም ውስጥ እየታየ መሆኑን ለአብነትም ጥምቀት ላይ የሚታዩ መፈክሮችን ካብራሩ በኋላ አክራሪዎቹ “አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱትን ግልባጭ ሲያራምዱ ታይተዋል” ሲሉ የእስልምናው “ሰለፊ” በክርስትናው በተለይም በኦርቶዶክሱ በኩል “ማኅበረ ቅዱሳን” ነው የሚል አንድምታ ያለው አጭር ነገር ግን ከባድ ኃይለ ቃል ተናግረው አልፈዋል። “አንዳንድ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት የሚያራምዱት” ያሉት ግን ምን መሆኑን በርግጥ አላብራሩም። ምናልባት ከላይ “አንድ አገር – አንድ ሃይማኖት” የሚል መፈክር ያዙ የተባሉት የጥምቀት አክባሪዎች “የማኅበረ ቅዱሳን አባላት ሳይሆኑ አይቀሩም/ ናቸው” በሚል እሳቤ የተናገሩትም ይመስላል። ወደ ኋላ እንመለስበታለን።
በመጀመሪያ “አንድ ሃይማኖት” የሚለው መሠረታዊ ሐሳብ ለብዙ ውይይቶች በር የሚከፍት ትልቅ ጉዳይ ነው። ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚያስተምረን እና የጥምቀት አክባሪ ክርስቲያኖች በቲ-ሸርቶቻቸው ላይ አትመውት በፎቶግራፍ የተመለከትኩት ኃይለ ቃል ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ምዕራፍ 4 ቁጥር 5 ላይ የጻፈው “አንድ ጌታ፣ አንድ ሃይማኖት፣ አንዲት ጥምቀት” የሚለው ሐዋርያዊ ቃል ነው። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል እንጂ የጥምቀት አክባሪዎቹ የፈለሰፉት አይደለም። በዚህ የሐዋርያው ቃል ውስጥ ያለው “አንድ ሃይማኖት” የሚለው አገላለጽ የሚናገረው ስለ ክርስትና ሃይማኖት ነው። ሌሎች እምነቶች የሉም፣ መኖርም የለባቸው የሚል የጨፍላቂነት ትምህርት አለመሆኑን ሊቃውንቱ አምልተው አስፍተው ሲያስተምሩ ኖረዋል፤ እያስተማሩም ነው። አሁን ደርሶ የሚለወጥ ነገር የለም።
በኢትዮጵያ ዐውድ ከተመለከትነው “ክርስቲያኖች ኢትዮጵያ የምትባለው አገር የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች ብ….ቻ ናት፣ ያለ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሌሎቻችሁ ቦታ የላችሁም ትላላችሁ” የሚል አንድምታ እየሰጡ የሚናገሩ እና የሚጽፉ ብዙ ኢትዮጵያውያን ከመኖራቸው አንጻር “አንድ ሃይማኖት” የሚለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል አንዳንድ ሰዎች የተሳሳተ ትርጉም እንዳለው አድርገው እየተጠቀሙበት እንዳይሆን ሥጋት አለኝ።
“አንድ ሃይማኖት” የሚለው አገላለጽ ከሃይማኖት ጋር በማይተዋወቁ ሰዎች ዓይን ከተመለከትነው መቻቻልን ለማስተናገድ ፈቃደኝነት የጎደለው አገላለጽ ሊመስል ይችላል። መቻቻል ማለት ግን መሠረታዊ የራስን ሃይማኖት አስተምህሮ መናድና መካድ ስላልሆነ መፍትሔው እርስ-በርስ መገነዛዘብና መረዳዳት ነው። የትኛውም ክርስቲያን “አንድ ሃይማኖት” ቢል የሐዋርያውን ቃል መጥቀሱ እንጂ ሌላ እምነት ላላቸው ኢትዮጵያውያን ጥላቻ አለው ማለት አይደለም። የጥምቀት አክባሪ ወጣቶች ቲ-ሸርቶች ላይ የተጻፈውን የሐዋርያውን ቃል የምረዳው በዚህ መንፈስ ነው።
ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የጠቀሱት መፈክር “አንድ ሃይማኖት” ብቻ ብሎ ሳያበቃ “አንድ አገር” የሚለውን ጨምሮበት “አንድ አገር – አንድ ሃይማኖት” በሚል ተጽፎ ከሆነ አባባሉ ሌላ ትርጉም ማለትም “የክርስቲያን መንግሥት ለመመሥረት መሻት” የሚል አንድምታ ሊሰጠው ይችላል። ቲ-ሸርቶችን የለበሱ እና ባነሮችን የያዙ ወጣቶች በጥምቀት በዓላት አሁን ባለው መልክ በዓል ማክበር ከጀመሩ ገና ሁለት ወይም ሦስት ዓመታቸው ነው። በነዚህ ሁለት ወይም ሦስት ዓመታት የጥምቀት በዓላት ላይ የተነሱ እና ከተለያዩ ድረ ገጾችና ማኅበራዊ ገጾች የሰበሰብኳቸውን ከአንድ ሺህ አምስት መቶ በላይ ፎቶግራፎች በድጋሚ በጥንቃቄ ለመመልከት ሞክሬያለኹ። እነዚህ በተለያዩ ካሜራዎች፣ በተለያዩ አንሺዎች፣ ከተለያዩ አቅጣጫዎችና በተለያዩ ቦታዎች ከተነሡት ፎቶግራፎች ውስጥ ጠ/ሚኒስትሩ ያሉትን ዓይነት ጥቅስ ወይም ተመሳሳዩን ፈልጌ ላገኝ አልቻልኩም። በርግጥ መፈክሩ በነዚህ ፎቶዎች ውስጥ ባለመገኘቱ የተነገረው ነገር ስህተት ነው ማለት ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ከመፈክሩ ከባድነት እና ከያዘውም ሐሳብ ጽኑዕነት አንጻር አንዱም ፎቶ አንሺ ሊያነሳው ያለመቻሉ ሁኔታ የአጋጣሚ ብቻ ነበር ለማለት አያስችልም። ስለዚህ አስቀድሞም ኅሊናዬ እንደሚነግረኝ እንዲህ የሚል ጥቅስ አልነበረምም አልተጻፈምም ለማለት እደፍራለኹ።
“አንድ አገር” የሚለውን ነጥብም በተመለከተ ባለሙያዎች የበለጠ ሊያብራሩት እንደሚችሉ ባምንም በግሌ የሚሰማኝን ግን በአጭሩ ለመጠቆም እሞክራለኹ። እዚህ በምንኖርበት አገር በአሜሪካ Pledge of Allegiance የሚሉትና ቃል ኪዳናቸውን የሚያጸኑበት መሐላ (ማለትም “I pledge allegiance to the flag of the United States of America, and to the republic for which it stands, one nation under God, indivisible, with liberty and justice for all”) አላቸው። አሜሪካዊ የሆነ ሁሉ ከትንንሽ ተማሪዎች እስከ ምክር ቤት አባላት ድረስ ያውቁታል፣ በየአጋጣሚውም ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ይሉታል። ለአገራቸው ያላቸውንም ቃል ኪዳን ይገልፁበታል።
አንድ አገር/ one nation under God ያሉት ግን የሁሉም የሆነ አገር ማለታቸው መሆኑ ግልጽ ነው። አገር የጥቂቶች ብቻ ሳይሆን የሁሉም ዜጋ ሊሆን ይገባዋል። ኢትዮጵያን በምሳሌነት ካነሣን በአንዲቱ አገራችን ውስጥ ኢትዮጵያውያን ለብዙ ሺህ ዓመታት በሰላም እንደኖርነው ሁሉ አሁንም ክርስቲያኑም፣ ሙስሊሙም፣ የሚያምነውም የማያምነውም “አገሬ” ብሎ ሊኖርባት ይገባል እንጂ ለዚህኛው እምነት ተከታይ “አገር” ሆና ለሌላው እምነት ተከታይ ደግሞ አገር የማትሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።
“አንድ አገር” ሲባልም ሥጋት የሚገባው ዜጋ ሊኖር አይገባም። “አንዲት አገር” ዜጎቿ ተጨፍልቀው፣ ተጠፍጥፈው የምትፈጠር አይደለችም። በሌላ ጽሑፍ እንዳነሣኹት ኢትዮጵያውያን ብዙዎች ብንሆንም አንዲት አገር ናት ያለችን። አገራችን ቀለማችንና ቋንቋችን ለየቅል ቢሆንም ሁላችን በአንድነት የምንኖርባት የጋራ ቤታችን ናት። ኢትዮጵያውያንም እንደ አሜሪካኖቹ “ከፈጣሪ በታች ያለች አንዲት አገር/ one nation under God” አለችን ብንል የሚያሳፍር አይሆንም። በእርሷ ነውና እኛም “ኢትዮጵያውያን” የተባልነው። በሃይማኖትም አንጻር ካየነው ይህቺ አገራችን ቅዱሳን በኪደተ እግራቸው የባረኳት፣ አበው በደማቸው የጠበቋት፣ እምነት እና ቋንቋ ሳንለይ የምንኖርባት ቅድስት ምድር ናት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እግረ መንገዳቸውን ያነሱትን እና በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን “አክራሪነት” በክርስቲያኑ በኩል “ይወክልልናል” ብለው የጠቀሱትን ማኅበረ ቅዱሳንን በተመለከተ እኔም እንደ አንድ አባል የማምንበት አቀርባለኹ። ማኅበሩ በኃላፊዎቹ በኩል የሚሰጠው መልስ እንደተጠበቀ ሆኖ ለሁለት አሥር ዓመታት አባል የሆንኩበት እና መንፈሳዊ እና ማኅበራዊ አገልግሎቶችን በመስጠት በሁሉም ዘንድ የተመሰከረለት ማኅበር “አክራሪ” አለመሆኑን በግሌ ለመመስከር እገደዳለኹ።
ማኅበረ ቅዱሳን “እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከበርበት” ማኅበር ሲሆን አገልግሎት መስጠት ከጀመረ እነሆ 20 ዓመት ሆነው። ማኅበሩም ያለውን ዓላማ፣ ግብና ርዕይ በመጽሔቶቹ፣ በጋዜጦቹ፣ በዐውደ ርእዮቹ፣ በኦዲዮ እና ቪዲዮ ውጤቶቹ ደጋግሞ ጽፏል፣ ተናግሯል፣ አስተምሯል። ከዚህ አንጻር ማኅበሩ አገርንም ሆነ ፖለቲካን፣ ሌሎች እምነቶችንም ሆነ ተቻችሎ መኖርን በተመለከተ ከማንም በላይ በሰፊው፣ በበሰለ እና ጤናማ በሆነ መንገድ ሐሳቡን አስተጋብቷል። ስለዚህም የማኅበረ ቅዱሳን አቋም “ጥምቀት ላይ የወጡ ጥቂት ሰዎች ይዘዋቸው ነበር” በተባሉ መፈክሮች የሚገለጽ አይደለም። በነዚህ 20 ዓመታት የተሠሩ ሥራዎቹን፣ የሕትመት ውጤቶቹን እና አባላቱ በግልጽም ሲናገሩት የኖሩትን መመርመር በርግጥም ማኅበሩ ምን ዓይነት ነጽሮተ- ዓለም (Weltanschauung) እንዳለው በቅጡ ለመረዳት ያስችላል።
ታዲያ “ማኅበረ ቅዱሳንን ከአክራሪነት ጋር ማገናኘት” ለምን አስፈለገ የሚለው ግን በደንብ መታየት አለበት። መንግሥትም የዚህን አስተሳሰብ ምንጭ መረዳት አለበት ብዬ አምናለኹ። መነሻው ቤተ ክርስቲያናችንን የእርሷ ባልሆነ ትምህርት እና እምነት ለመለወጥ የሚሞክሩ ነገር ግን “ይህንን እንዳናደርግ ማኅበረ ቅዱሳን እንቅፋት ሆኖብናል” የሚሉ አካላት (ተሐድሶዎች) ለረዥም ዘመን ሲያሰሙት የቆዩት ክስ ነው። በእነርሱ አስተያየት አንድ ሰው ኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮውን አልለውጥም ካለ “አክራሪ” ይሉታል። እነርሱ “አክራሪ ነው” የሚሉትን ሰው በሙሉ ጠቅልለው በጋራ “ማኅበረ ቅዱሳን” ብለው ይጠሩታል። ሰውየው የማኅበሩ አባል ቢሆንም ባይሆንም ለቤተ ክርስቲያኑ ጥብቅና የሚቆም ከሆነ ማሸማቀቂያቸው “ማኅበረ ቅዱሳን ነህ እንዴ?” የሚል ነው።
እንግዲህ በኦርቶዶክሳውያን እና በተሐድሶዎቹ መካከል ሲደረግ የቆየው ትግል አዲስ ምዕራፍ የሚያገኘው እነዚህ ኦርቶዶክስን ለመከለስ (ለማደስ) የሚፈልጉ ሰዎች “በፖለቲካው ጉያ ምቹ ቦታ ባገኘን” የሚለው ሙከራቸው ተሳክቶ በራሱ በመንግሥት ስም ዓላማቸውን ማራመድ ከጀመሩ ነው። ከነዚህም አብዛኞቹ የኢሕአዴግ የፖለቲካ መስመር ደጋፊዎች በመምሰል (በተለይም ከ1997 ዓመተ ምሕረቱ ምርጫ – ምርጫ ’97) እና ውዝግቡ ጀምሮ ማኅበረ ቅዱሳን ለቅንጅት ማሸነፍ ትልቅ ሚና ተጫውቷል በማለት በመንግሥት ልምጭ የራሳቸውን ዱላ ለማሳረፍ በብዙ ሲጥሩ እንደነበር ይታወቃል። በይፋም ጽፈዋል። የጠ/ሚኒስትሩ አጭርና ብዙ መልእክት የተሸከመች ዐረፍተ ነገር “እነዚያ መንግሥትን ተገን አድርገው ቤተ ክርስቲያኒቱን ፕሮቴስታንታዊ ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች/ ተሐድሶዎች መንግሥትን ለዓላማቸው መጠቀሚያ ለማድረግ የሚያደርጉት ጥረት ተሳካላቸው ማለት ነው?” የሚል ስሜት ያጭራል።
ከዚህ አንጻር ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ የወጣ እምነት ይዘው ቤተ ክርስቲያኒቱን እና ትምህርቷን በመለወጥ የራሳቸው ለማድረግ የሚሞክሩ ሰዎች፣ ቡድኖች እና ድርጅቶች መኖራቸው እየታወቀ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ እና በዕውቀቱ ለቤተ ክርስቲያኑ ብቻ ሳይሆን ለአገሩም በቅንነት የሚያገለግለውን አንድ ትውልድ ጨፍልቆ በአክራሪነት ስም መፈረጅ በቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ላይ ትልቅ የሚዛን መናጋት ያስከትላል ብዬ በድፍረት መናገር እችላለኹ። ተሐድሶዎቹም ሆኑ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቀናቃኞች “ዓላማችንን ሊያውቅብን ይችላል” የሚሉትን ማኅበር ሕጋዊ አገልግሎት ያለ አግባብ ሌላ ስም መስጠት ይህንን ቃል እንደ መመሪያ ወስደው የግል ፍላጎታቸውን ለመፈጸም ለሚቋምጡ ወገኖች ትልቅ ደስታ ነው።
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን እምነት አክራሪነትን መሸከም አይችልም። ሌላ ማንም አካል ሳያስፈልጋት ራሷ ቤተ ክርስቲያን የእርሷ ያልሆኑትን ለመለየት ችሎታ አላት። አማኞቿም ማን አክራሪ እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ። በበግ ለምድ ተደብቀው ሌሎችን “አክራሪዎች ናቸው” በሚል ሽፋን በጎች-ምእመናንን ለመንጠቅ የሚሞክሩትንም ያውቃል። የአክራሪነትን ምንነት ለመረዳት ሰፕቴምበር 11ን፣ የሎንዶኑን የባቡር ጣቢያ ፍንዳታ፣ የጅማውን ጭፍጨፋ፣ የኒው ዴልሒን የሽብር አደጋ፣ አል-ሸባብ በየጊዜው በሶማሊያ የሚፈጽመውን መመልከት ያስፈልጋል። ትርጉሙና ምንነቱ ይህ ሆኖ ሳለ ያለቦታው ይህንን ቃል መጠቀም ሕዝቡ ቃሉ ያዘለውን ቁምነገር እንዳይረዳ ከሚያደርገው በስተቀር ውጪ ሌላ ምንም ጥቅም የለውም።
በርግጥ ገዳማትንና አብነት ት/ቤቶችን ከጥፋት መታደግ አክራሪነት ነውን? ወጣቱ ትውልድ ሃይማኖቱን አውቆ በሥነ ምግባር ታንጾ አገሩንና ቤተ ክርስቲያኑን በቅንነት እንዲያገለግል ማድረግ አክራሪነት ነውን? በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ በነጻ የትውልድ ኃላፊነቱን ለመወጣት የሚሞክር ትውልድ መፍጠር አክራሪነት ነውን? በጭራሽ!!! ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለ ማኅበሩ ባሉት ሐሳብ አልስማማም።
ከላይ በመግቢያዬ በጠቀስኹት መጽሐፍ ላይ በዝርዝር ለመቅረብ እንደሞከርኹት “አክራሪነት”ን በማይገባው ምሳሌ መግለጽ በሕዝቡ አእምሮ ውስጥ ሊፈጥረው የሚችለው ሥዕል ዞሮ ዞሮ አገሪቱ ከአክራሪዎች ሊገጥማት የሚችለውን አደጋ ይጨምረዋል ብዬ አስባለኹ። ምክንያቱም ‘አክራሪነት’ አስቀያሚ መልኩን በኒውዮርክ ፍንዳታ ፍንትው አድርጎ ስላሳየ ዛሬ ማኅበረ ቅዱሳንን በዚህ ስም መጥራት በራሳቸው በወሐቢያ አክራሪዎቹ ዘንድ ሳይቀር የማይሆን ግምት ያሰጣል።
በአጠቃላይ ክቡር ጠ/ሚኒስትሩ የተናገሩት አጭር አስተያየት ለተለያዩ ዓይነት ትርጉሞች ክፍት ቢሆንም ይህንኑ ንግግራቸውን ከሕግ እና ከመመሪያ የሚቆጥሩ ብዙ ክፍሎች የንግግራቸውን ጫፉን ብቻ ይዘው ሙሉ መንፈሱን ሳይረዱ የመሰላቸውን አቅጣጫ እንዳይሄዱ ጥንቃቄ መደረግ አለበት። በጠቅላላውም ካየነው የማኅበረ ቅዱሳን ጉዳይ መታየት ያለበት “በቤተ ክህነቱ እና በቤተ ክህነቱ ብቻ” ነው ብዬ አምናለሁ። በሃይማኖት ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት ማለት የቤተ ክርስቲያኒቱን ጉዳይ ለራሷ መተው ነው።
በሌላም በኩል የሙስሊሞችን ጉዳይ ለሕዝብ ለማሳየት እና ቀሪው ሕዝበ-ሙስሊም እንዳይከፋ በሚመስል መልክ ከክርስቲያኑ ወገን ማኅበረ ቅዱሳንን በማነጻጸሪያነት መጥቀስ ተገቢ ነው ብዬ አላምንም። የሙስሊሞቹን ጉዳይ በራሳቸው ዐውድ እና በራሳቸው የእምነት ሥርዓት መፍታት እንደሚገባው ሁሉ የክርስቲያኑንም ጉዳይ በክርስትና ሃይማኖት ሕግ እና በክርስትና መነጽር ብቻ ሊታይ ይገባዋል።
ይቆየን
ፀሐፊውን ለማግኘት፦
ephremeshete@Gmail.com
http://www.adebabay.com/
No comments:
Post a Comment