Total Pageviews

Tuesday, October 9, 2012

EPRDF - D ማናቸው?

የዚህን ጥያቄ ምላሽ ለማወቅ የማይጓጓ አለ ለማለት አይቻልም። ምክንያቱም ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ለማየት የሁላችንም ምኞት ነው። ይህ ዜና እውነት ከሆነ የአፍሪቃ ቀንድን የፖለቲካ የሃይል አሰላለፍ ሙሉ በሙሉ የሚለውጥ ክስተት ሊፈጠር ይችላል። ማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት እና ማንኛውም ዜጋ ወደ ሃገሩ እንዲገባ አዋጅ ይታወጃል። ህዝብ የመረጠው የሚነሳበት፣ ያልተመረጠ የሚሰናበትበት ስርአት ይፈጠራል። ሚዴያዎች ነፃ - የፖለቲካ እስረኞች ወደቤት።

ከዚያም የፓርላማውን ውይይት ማዳመጥ፣ እንደ ተወዳጅ ተከታታይ ፊልም የሳምንቱ አጓጊ ክስተት መሆን ይጀምራል። ስብሃት ነጋ፣ ብርሃኑ ነጋ፣ እስክንድር ነጋ፣ እያሱ ነጋ (አለማየሁ)፣ ነገደ ጎበዜ፣ ሌንጮ ለታ፣ ነጋሶ ጊዳዳ እና ስዬ አብርሃ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው ሲሟገቱ እንሰማለን። የአባይ ግድብ ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል። ወያኔ ያቀደው ኢትዮጵያ ባቡር መንገዶች እቅድ ይበልጥ ተስፋፍቶ ይገነባል። በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ሰላም ወርዶ፣ በህዝቦች መካከል እንደ ጥንቱ “እትዬ እንትና ኑ ቡና ጠጡ” መባባል ይጀመራል። በርግጥም ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ቢሆን፣ በአንድ አዳር የሚሊዮናት ህይወት መለወጥ በጀመረ።
 
EPRDF – D የላከውን ደብዳቤ ሳነብ ከላይ ያለውን ነበር ያሰብኩት። ወዲያው ግን ከቀን እንቅልፌ ባነንኩ። ደብዳቤውንም ሆነ መግለጫውን ደግሜ አነበብኩት።

Dear Media members,
The new EPRDF Democratic (EPRDF D) has been established. Please find our Press Release attached. The obsolete and un-reforming EPRDF is decaying. For all party related correspondences, we will notify you with our new contact details as soon.

Best Regards,
EPRDF D Leadership Organizing Committee
J.S.

“J.S.” ማነው? በእነዚህ ፊደል የሚጀምር ስም ያለው ሰው ለማግኘት ሞክሬ ነበር። ‘የኮድ ስም ይሆናል’ ብዬ አሰብኩ። ሰዎቹ በቅርቡ ማንነታቸውን የሚገልፁ ከሆነ ግን ስሙ የኮድ ላይሆንም ይችላል። ለነገሩ በዚህ ስም የሚጠሩ ሰዎች ሶስት ብቻ ነው ያስታወስኩት። እነርሱም፣ ጃማይካ፣ ጃምቦ ጆቴ፣ እና ጃራ አባገዳ ናቸው። ጃማይካ ህወሃት ነው። ጃምቦ ዘፋኝ ነው። ጃራአባገዳ ኢህአዴግ አይደለም። ሶስቱም ከአጭር ማስታወሻዬ ላይ ተሰረዙ። መግለጫው

'We, the no- TPLF member parties and allies of EPRDF today, are under the full control of the TPLF and it arbitrarily meddles in our internal workings.' ስለሚል በቡድኑ ውስጥ የህወሃት ሰዎች የሉበትም ማለት ነው።

ዝቅ ብሎ ደግሞ እንዲህ ሲል ፍንጭ ይሰጣል።

'The hardcore and extremist sects of the EPRDF have so far paid deaf ear to our requests and at times fired most of our colleagues labeling them “opposition aficionados and neo-liberals”.'

ኢህአዴግ መቼም በዚያም መጣ በዚህ ምስጢር ይወዳል። ስለዚህ እንደፈረደብን ለመገመት እንገደዳለን። እነ ፃድቃን፣ እነ አለምሰገድ እነ ተወልደ “ህወሃት” ስለሆኑ ከግምታችን ውጭ ናቸው። ከኦህዴድ መካከል ውጭ አገር ያሉትን አሰብኩ። አልማዝ መኮ፣ ሃሰን አሊ፣ ዮናታን ዲቢሳ፣ ሶስቱም አይሆኑም - ቻዎ! ከብአዴን ማን አለ? ተሾመ አስራትና ጌታቸው ሃይሉ? እነዚህ ሰዎች የት እንዳሉ እግዚአብሄርም አያውቅ። ጌታቸው እንኳ በስህተት ነበር ማእከላዊ ኮሚቴ ያደረጉት። ደንግጦ በዚያው ጠፍቶ ቀረ። ተሾመ አቅም ነበረው። ባልታወቀ ምክንያት ዝምታን መረጠ። እነዚህ አይሆኑም። በቅርቡ የኮበለለው ከፍያለው አዘዘ? አይመስለኝም። ከደኢህዴግ የኮበለለ የማውቀው ሰው የለም። ስለዚህ በጥቅሉ ከደጅ ማንም የለም፣ አልኩና አሳብ ፈረሰኛውን፣ “ቼ” አልኩት። “ቼ! ፈረሴ! ቁና ገብሴ፣ ገለባ ልብሴ፣ መሬቴ ዋሴ!” እያልኩ እንደ አድአ ባለቅኔዎች ብአዴንን አሰስኩት። በረከት፣ ገነት፣ ሃይሌ፣ አዲሱ፣ አያሌው፣ ፍሬህይወት፣ ህላዌ፣ ወንደሰን፣ ሰለሞን፣ ታደሰ፣ አንዳቸው ላይ እንኳ መቆም አቃተኝ። ዳዊት ዮሃንስ ላይ ልጓም ይዤ ነበር። ዳዊት ታሞአል። በጋሪ እየተገፋ እንደሚሄድ ነግረውኛል። ኤርትራውያን ተቃዋሚዎች ለመለስ ስንብት ግዮን ሆቴል ባዘጋጁት ስነስርአት ላይ እንኳ የተገኘው በሰዎች ድጋፍ ነው። ስለዚህ ዳዊት አይሆንም።

ወደ ደቡብ እና ኦሮሚያ ሰዎች ተሻገርኩ። ሬድዋን፣ ሙክታር፣ ተሾመ ሙላቱ፣ ግርማ ብሩ፣ ካሱ ይላላ፣ ኩማ፣ አባዱላ፣ አስቴር፣ አበራ፣ ጁነዲን ሳዶ? J.S. ወይ መከራ? ድካም ብቻ። ዝቅ ያሉ ካድሬዎችን ለማሰብም አልቃጣሁ።

ኢህአዴግ ቆቅ የሆነ ድርጅት ነው። ከአመራሩ በታች በከፍተኛ ካድሬ የሚመድባቸው በሙሉ ማለት ይቻላል፣ ለማስፈፀም የማያመነቱ፣ የተፈተኑ ከተፎዎችን ነው። ፕሮፌሽናል የሚባሉትን ብዙም ሳያስጠጋ ብዙም ሳያርቅ፣ በከተፎዎች ቁጥጥር ስር ይይዛቸዋል እንጂ፣ የሴል ሰብሳቢ አያደርጋቸውም። ስለዚህ ርስበርስ ሊገናኙ የሚችሉበት ምንም እድል የለም። እና የሰዎችን ስም ባሰብኩ ቁጥር፣ “ቢልጡት ሽንኩርት” ሆነብኝ። “ቢልጡት ሽንኩርት - ቢልጡት ሽንኩርት፣ እንደገና ቢልጡትም ያው ሽንኩርት” ይል ነበር ስብሃት ገብረእግዚአብሄር ነብሱን ይማረውና።

ለነገሩ በረከት ስምኦን “መደበሪያ ይሁናችሁ፣ በተስፋ ያቆያችሁ” ብሎ የላከልን ሰበር-ዜና ይሆን? “ኢህአዴግ ተጎመደ፣ ተሰነጠቀ፣ እንደ ጣውላ፣ እንደ አለላ፣ አለቀለት፣ ሻንጣ እሰሩ፣” ስንባባል እነሱ ይስቁ ይሆናል። ማን ያውቃል? በረከት እንዲህ ያለ ቀልድ ይወዳል። ጎንደሬዎች እንኳ አጤ ቴዎድሮስ ሽጉጡን ከጠጣ ወዲህ ብዙ ቀልድ አያውቁም። በረከት ግን ደህና ነው። እና እያሾፈብን እንዳይሆን።

በርግጥ ከመነሻዬ እንደገለፅኩት ኢህአዴግ ዴሞክራሲያዊ ቢሆን የምንመኘው ነው። በነፃ ግን የሚገኝ አይመስለኝም። ከዝሆኑ ላይ የስጋ ቁራጭ ይወድቅ ይሆናል በሚል ስትከተል እንደኖረችው ቀበሮ እንዳንሆን እሰጋለሁ። ይህን የሰሞኑን ደብዳቤም በቁምነገር ልወስደው አልቻልኩም። “D” በመጨመር “ተገንጥያለሁ” የሚለውን ነገር የጀመረው ኢህአፓ ነው መሰለኝ። ኢህአፓ ምን ያልጀመረው ነገር አለ? ከኢህአፓ “D” በሁዋላ እንኳ፣ ስንት “D” ተመልክተናል? ቅንጅት“D” ፣ ኦብኮ“D” ፣ ኦርቶዶክስ“D” ፣ መጅሊስ“D” ፣ ታላቁ ሩጫ“D”፣ ኦነግ“D” ፣ ግንቦት 7“D” ፣ እግዜር ይቅር ይበለን። “D” የተባሉ የከሰሩ ፖለቲከኞችን ዲክታተር ከመሆን እግዜር ይጠብቃቸው። “ካልበላሁት ልበታትነው” ከተባለው መንፈስ ይሰውራቸው። በእኔ በኩል እምነቴ የተለየ ነው። ከቻሉ ከእናት ድርጅታቸው ሳይወጡ ከውስጥ ሆነው ቢታገሉ፣ ካልቻሉ ግን የራሳቸውን አዲስ ራእይ ነድፈው፣ የራሳቸውን አዲስ ስም ቢያስተዋውቁ ይመረጣል።http://www.tgindex.blogspot.no/2012/10/eprdf-d_9.html#more

No comments:

Post a Comment